ቱሪዝም ኢትዮጵያ በመንፈቅ ዓመት ዕቅድ ክንውን አፈጻጸም ላይ ተወያየ

(ቱኢ)ቱሪዝም ኢትዮጵያ የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ ክንውን አፈጻጸምን በተመለከተ ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ውይይት አደረገ፡፡ በስብሰባው ላይ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡ አቶ ስለሺ ግርማ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት ቱሪዝም ኢትዮጵያ ባለፈው መንፈቅ ዓመት በርካታ ስራዎችን ያከናወነ ቢሆንም በቱሪዝም ዘርፍ መሰራት የሚገባቸው በርካታ ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ተቋሙ አዲስ መዋቅር አጸድቆ የሰው ኃይል በማሟላት ወደ ተግባር መግባቱን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተደራሽነት እየሰፋ መምጣቱን፣ኮሮና ቫይረስ የቱሪዝምን ዘርፍ ባጠቃበት በዚህ ወቅት ባለ ድርሻ አካላትን በመደገፍና ተለዋዋጭ የሆኑ ዕቅዶችን በማውጣት የሚያበረታታ ስራ መሰራቱን አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮና ማይስ ኢትዮጵያ አዲስ ብራንድ፤የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካዮች፣ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ አባላት፣ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በሚገኙበት ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ይፋ የማድረግ ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ አቶ ሀብታሙ አድማሱ የዕቅድ፣በጀት፣ዝግጅትና ክትትል ግምገማ ዳይሬክተር የመስሪያ ቤቱን የ6 ወራት ዕቅድ ክንውን ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ሀገራችንን በተለያዩ ሁነቶች ለማስተዋወቅ ሀገር ውስጥና ውጭ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ስራዎች ተሰርቷል፡፡ ተጨማሪ ስምንት አዲስ መዳረሻዎች፡- ጨበራ ጩርጩራ፣ ታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ ጋምቤላ፣ ገራይሌ ፣ሶፍ ኦመር ዋሻ፣ጢስ ዓባይ፣ዓባይ ግድብ እና ቢጅሚስ ብሔራዊ ፓርኮች በጥናት ተለይተው ለእነዚሁ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልዩ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እንዲፈቀድ በመሰራት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ፣ መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ቱሪዝም ኢትዮጵያና ባለ ድርሻ አካላት ይህን ምቹ አጋጣሚ ለመጠቀም በትጋት መስራት ይገባቸዋል በማለት አቶ ስለሺ ግርማ ግርማ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Leave a Comment